አካዳሚያዊ የሥነ ምግባር ደንብ

የትምህርት ክፍል ደንቦች እና መመሪያዎች

ከክፍል የሚጠበቁ ነገሮች

የክፍል ጊዜዎ ዋጋ ያለው ነው። የሚከተሉት ፖሊሲዎች እርስዎ የሚደገፉበትና ስኬታማ የመሆን እድል የሚያገኙበትን አወንታዊ የመማሪያ ሁኔታ ያረጋግጣሉ።

SEIU 775 Benefits Group ከፍተኛ ጥራት ካለው ሥልጠና እና የሙያ ማሻሻያ ጋር ለረዥም ጊዜ የሚሠሩ እንክብካቤ ሰጪ ሠራተኞችን እና ደንበኞቻቸውን ሕይወት ለማሻሻል ዓላማ ሰንቆ ይንቀሳቀሳል። ተማሪዎችን፣ አሠልጣኞችን እና ሠራተኞችን ላቅ ያለ አካዳሚያዊ ሥነ ምግባር እና ተአማኒነት እንዲኖራቸው እንፈልጋለን። 

 

ከተማሪዎቻችን የምንጠብቃቸው ነገሮች እነዚህ ናቸው፦

  • ታማኝነት። 
  • አደራ ጠባቂነት። 
  • አክብሮት። 
  • ፍትሓዊነት። 
  • ኃላፊነት።
  • ሙያዊ ብቃት።  

SEIU 775 Benefits Group ለሁሉም ሰዎች የብዝሓነትን፣ የርትዓዊነትን እና የአሳታፊነትን ዕድል ለማጎናፀፍ ፅኑ አቋም አለው። የረቀቀ ዘረኝነትን፣ ይህንን የሚያባብሰውን የመብት ጥሰትን እና እንዲባበስ በእጅ አዙር የሚያበረታታውን አመራር ለመታገል ጥቁር እና ጠይም መልክ ያላቸው ማኅበረሰቦች በሚያደርጉት ትግል ላይ ከጎናቸው በመቆም እንታገላለን። የጥቁሮች ሕይወት ፋይዳ አለው። ለደኅንነት አስተማማኝ በሆነ አካባቢ ውስጥ የመኖር መብት አልዎት። ይህንን መብት የሚጥስን ማናቸውንም ዓይነት ባሕሪ አንታገሥም። SEIU 775 Benefits Group ነጭ ካልሆኑ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጎን ይቆማል። የዘር መድልዎ እና የጥላቻ ንግግርን ጨምሮ ማናቸውንም ዘረኝነት ወይም የዘር ጭቆናን የሚያንጸባርቅ ባሕሪ በጭራሽ አንታገሥም። ይህንን የሚጥስ ማናቸውም ሰው ከመማሪያ ክፍሉ እንዲወገድ ይደረጋል። ዘረኝነትን መዋጋት የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት ነው። ዘረኛ የሆነ ማናቸውንም ዓይነት ባሕሪ ከተመለከቱ፣ እባክዎ ዝም ብለው አይለፉት፤ ለአሠልጣኝዎ በአፋጣኝ ሁኔታውን ያሳውቁት።

አስፈላጊውን ዝግጅት ያድርጉ 

እባክዎ:

  • ከትምህርት መጀመሪያው ቀን በፊት ለሥልጠና ለመመዝገብ የእኔ ጥቅሞችን ይጠቀሙ። ቀደም ብለው በተመዘገቡ ቊጥር፣ ይበልጥ የመማር ዕድል አማራጮችን ያገኛሉ። የጊዜ መርሐ ግብር አወጣጥ ላይ እገዛ የሚያስፈልግዎት ከሆነ የአባል መረጃ ማዕከሉን /Member Resource Center (MRC)/ ወይም የእርስዎን ኤጀንሲ የሥራ ቀጣሪ ያነጋግሩ።
  • የሚማሩባቸው ክፍሎች የት ቦታ እንደሚገኙ ይወቁ። 
  • ወደ መማሪያ ክፍሉ እንዴት እንደሚሄዱ እና እንደሚመለሱ የራስዎን ዕቅድ ያዘጋጁ።
  • ለትምህርት ለመመዝገብ ሲመጡ በመንግሥት የተሰጠ ፎቶ ያለበት ማንነትን የሚገልጽ መታወቂያ ይዘው ይምጡ። ይህ የስቴት የነዋሪ መታወቂያ ወረቀት፣ የመንጃ ፈቃድ ወይም ፓስፖርት ሊሆን ይችላል።
  • ማስታወሻ ደብተር፣ እስኪብርቶዎች እና ሌላ የጽሕፈት መሣሪያዎችን ይዘው ይምጡ። ትምህርቱ በሚጀመርበት የመጀመሪያ ቀን ላይ የመማሪያ ቁሳቁሶችን ይቀበላሉ።
  • እንደ ኮምፒውተር፣ ታብሌት ወይም ስማርት ስልክ የመሳሰሉ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ለመጠቀም ራስዎን ያዘጋጁ። ኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ከሌልዎት፣ ከSEIU 775 Benefits Group በተውሶ መልክ ማግኘት ይችላሉ።
  • የቋንቋ እገዛ ለአካል ጉዳተኝነት የሚሰጡ, አገልግሎቶች ወይም ሌላ ድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚያስፈልግዎት ከሆነ MRCን ያነጋግሩ።

 

የሚጠበቁ ነገሮች:

ንቁ ተሳትፎ

እባክዎ:

  • ለተሳትፎዎ ዕውቅና እንዲያገኙ ሁሉንም ትምህርት ይከታተሉ።
  • በማናቸውም ጊዜ አሠልጣኞችን፣ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን እና ሌላ ተማሪዎችን በአክብሮት ያስተናግዷቸው።
  • የመማሪያ ክፍል መገልገያዎችን በጥንቃቄ ይያዙ እንዲሁም ያገኙበት ቦታ ይመልሱ። የተዝረከረኩ ነገሮችን ያፅዱ እንዲሁም ቆሻሻን በቆሻሻ መጣያ ውስጥ ይጣሉ።
  • በንቃት ያዳምጡ እንዲሁም አላስፈላጊ ሁከትን ከመፍጠር ይቆጠቡ።
  • በግል እና በቡድን የሚሰጡ መልመጃዎችን ሙሉ በሙሉ ሠርተው ያጠናቁ። 2 ወይም ከዚያ በላይ ሰዎችን የሚያሳትፉ እንቅስቃሴዎች በቡድን የሚሠሩ ይሆናሉ።
  • ሁሉንም የበይነመረብ /ኦንላይን/ እና የክኅሎት መልመጃዎችን ሠርተው ያጠናቁ።
  • ተራዎ እስከሚደርስ ይጠብቁ እንዲሁም ሌሎች ሲናገሩ ያዳምጡዋቸው። 

በሰዓቱ ሳያረፍዱ መድረስ እና ሌሎች በክፍል ተገኝቶ የመማር ግዴታዎች

እባክዎ:

  • ዕውቅና ማግኘት እንዲችሉ ከትምህርቱ መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ ይፈርሙ። በአንድ ቀን ከአንድ ጊዜ በላይ በትምህርት መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ መፈረም ሊኖርብዎት ይችል ይሆናል።
  • በሰዓቱ ሳያረፍዱ ይድረሱ እና ከዕረፍት እና ከምሳ በኋላ በሰዓቱ ይመለሱ። ወደ መማሪያ ክፍልዎ ከ10 ደቂቃ በላይ አርፍደው ከደረሱ፣ ወደ መማሪያ ክፍሉ እንዲገቡ አይፈቀድልዎትም እንዲሁም ለዚህ የቀሩበት ክፍል የተሳትፎ ዕውቅና አያገኙም።
  • በመማሪያ ክፍል ተገኝቶ ለመማር የማይችሉ ከሆነ በተቻለ ፍጥነት ለ MRC ወይም ለእርስዎ ኤጀንሲ የሥራ ቀጣሪ ያሳውቁ። MRC ወይም የእርስዎ ኤጀንሲ የሥራ ቀጣሪ ያመለጥዎትን ትምህርት በሌላ ክፍለ ጊዜ ተገኝተው ማካካስ የሚችሉበትን መንገድ በማዘጋጀት ላይ ሊያግዝዎት ይችላሉ።
  • ወደ መማሪያ ክፍሉ ሌሎች ጎብኚዎችን፣ ደንበኞችን፣ ሕፃናትን ወይም የቤት እንስሳትን ይዘው አይምጡ (በአሜሪካ የእንስሳት መዝገብ — ADA መጠየቂያ ቅጽ የተሞሉ አገልግሎት የሚሰጡ እንስሳት ብቻ ይፈቀዳሉ)። የተመዘገቡ ተማሪዎች፣ የተመዘገቡ አስተርጓሚዎች፣ ፈቃድ የተሰጣቸው የማኅበረሰብ አስተርጓሚዎች እና ሠራተኞች ብቻ በመማሪያ ክፍሉ ውስጥ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል።

የግል ስልኮች

እባክዎ:

  • በትምህርት ወቅት የእርስዎን የእጅ ስልክ ድምፅ ያጥፉት። 
  • ትምህርት እየተሰጠ እያለ የስልክ ጥሪዎችን አያድርጉ ወይም የጽሑፍ መልእክት አይላላኩ።
  • የስልክ ጥሪዎችን ለማድረግ ሆነ ለመቀበል ወይም ሌላ የግል ጉዳዮችን ለማከናወን በመርሐ ግብሩ ላይ የተቀመጡትን የዕረፍት ጊዜዎችን እና የምሳ ሰዓትን ይጠቀሙ።

የአለባበስ ሥነ ሥርዓት

እባክዎ እንደሚከተለው ይልበሱ፦ 

  • ተገቢነት ያላቸው እና በክፍል ውስጥ ለሚያከናውኗቸው ተግባራት ምቹ የሆኑ ልብሶችን ይልበሱ።
  • ጠፍጣፋ፣ የማያንሸራትቱ፣ ድፍን ጫማዎችን ከካልሲ ጋር ያድርጉ (አጥብቆ ይመከራል)።

አጠቃላይ ደኅንነት

እነዚህ ነገሮች የተከለከሉ ናቸው፦ 

  • ጉልበተኝነት።
  • ሌሎችን ማዋረድ። 
  • በሚከተሉት ላይ ተመርኩዞ መድልዎና ማግለልን መፈጸም፦ 
    • ዘር። 
    • ዕድሜ። 
    • የቆዳ ቀለም። 
    • ብሔር። 
    • ጾታ። 
    • የወሲብ ዝንባሌ። 
    • የሥርዓተ ጾታ ማንነት። 
    • የሥርዓተ ጾታ አቋም። 
    • ሃይማኖት። 
    • አገር። 
    • የፍልሰተኝነት ሁኔታ። 
    • የአካል ጉዳተኝነት እና ችሎታ። 
    • የፖለቲካ ዝንባሌ። 
    • ወታደራዊ ታሪክ። 
    • ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መደብ።

እባክዎ እነዚህን ነገሮች ይዘው ወደ መማሪያ ክፍሉ እንዳይመጡ፦

  • የጦር መሣሪያዎች። 
  • አልኮል። 
  • አደገኛ መድኃኒቶች (አደንዛዥ ዕፅ)።

ኤሌክትሮኒክ ሲጋራ እና የሚታኘክ ትምባሆን ጨምሮ ሲጋራ ለማጨስ ለዚሁ ተብሎ በተከለለው ቦታ እባክዎ ይጠቀሙ። እነዚህን ነገሮች በተቋሙ ሕንጻ ውስጥ ወይም ከመግቢያ በሮቹ በ25 ጫማ ርቀት ውስጥ መጠቀም የተከለከለ ነው። 

ደኅንነትን እና ጸጥታን ለአደጋ የሚያጋልጥ ማናቸውም ባሕሪ በምንም ዓይነት በቸልታ አይታለፍም። SEIU 775 Benefits Group አዋኪ ተሳታፊዎችን ከተቋሙ ክልል ለማሰናበት ያለው መብት የተጠበቀ ነው። በመማሪያ ክፍሉ ውስጥ ደኅንነት የማይሰማዎት ከሆነ እባክዎ ለአሠልጣኝዎ ያሳውቁዋቸው።

 

እንደ ኮቪድ-19 የመሳሰለ ወረርሽኝ በሽታ በሚከሰትበት ወቅት በተጨማሪ የሚሰጡትን ደኅንነት የመጠበቂያ መመሪያዎችን ያክብሩ። እባክዎ:

  • ከታመሙ ወይም ሊታመሙ የሚችሉ መስሎ ከተሰማዎት ወደ መማሪያ ክፍሉ አይምጡ። በተለምዶ ከታወቁት የኮቪድ-19 የበሽታ ምልክቶች አንዳቸውም ቢሆን ከተሰማዎት፣ እባክዎ ለእርስዎ አሠሪ እና MRC የትምህርት ክፍለ ጊዜውን ወደ ሌላ ጊዜ እንዲያዛውሩልዎት ያሳውቁዋቸው። 
  • የእርስዎ ደንበኛ ወይም እርስዎ የቅርብ ንክኪ የነበርዎት ማናቸውም ሰው በኮቪድ-19 ከተያዘ ሰው ወይም ሌላ ማናቸውም ተላላፊ በሽታ ካለበት ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ከነበራቸው ለእርስዎ አሠልጣኝ ያሳውቋቸው።
  • ማናቸውም የበሽታ ምልክቶች ካሉብዎት ለእርስዎ አሠልጣኝ ያሳውቋቸው። ወደ ቤት ይላኩ እና ከMRC ጋር በመተባበር ትምህርቱን ወደ ሌላ ጊዜ እንዲያዛውሩ ይጠየቃሉ። 
  • በማናቸውም ጊዜ በክፍል ውስጥ ካለ ከሌላ ማንም ሰው ቢያንስ 6 ጫማ ርቀት ይጠብቁ።
  • እንደ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የመሳሰሉ የፊት መሸፈኛዎችን በክፍሉ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ በሙሉ ያድርጉ። እንደ ጓንት፣ መከላከያ መነፅር ወይም የፊት መሸፈኛ መስታውት የመሳሰሉ የግል ደኅንነት መጠበቂያ ቁሶችን ለአንዳንድ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ሊኖርብዎት ይችል ይሆናል።
  • የሙቀት ልኬትን ጨምሮ አስፈላጊ በሆኑ የጤና ምርመራዎች ላይ በፈቃደኝነት ይሳተፉ።
  • ሌሎች ማናቸውም በ SEIU 775 Benefits Group፣ በስቴት እና በአካባቢ ሕጎች ወይም ደንቦች የተቀመጡ የደኅንነት መጠበቂያ ግዴታዎችን ያክብሩ።

ከመማሪያ ክፍል ተቀርቶ መቼ በቤት መቀመጥ እንደሚያስፈልግ 

ከታመሙ ወይም እንደ የእንፍሉዌንዛ የመሰሉ የበሽታ ምልክቶች የሚታዩብዎት ከሆነ ወደ መማሪያ ክፍሉ አይምጡ። እንደ የእንፍሉዌንዛ የመሰሉ የበሽታ ምልክቶች ከነበሩበት ወይም ከባድ በሆነ ተላላፊ በሽታ እንደተያዘ በሕክምና ከተረጋገጠ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ከነበርዎት ወደ መማሪያ ክፍል አይምጡ።

ራስን ማዘጋጀት 

እባክዎ:

  • የማይረበሹበትን ጸጥ ያለ ትምህርት መከታተያ ቦታ ያዘጋጁ። 
  • ትምህርቱን በሚማሩበት ጊዜ ጸጥታ እንደሚያስፈልግዎት ለቤተሰብ አባላቶችዎ ይንገሩዋቸው።
  • ያልዎት መሣሪያዎች እና ትምህርቱን በሚከታተሉበት ጊዜ በሚገባ ሊሠሩ እንደሚችሉ አስቀድመው ያረጋግጡ። 
  • ትምህርቱን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ያክል ጊዜ ለማጥፋት እንደሚችሉ አድርገው ራስዎትን ያዘጋጁ። 
  • የቋንቋ እገዛ, ለአካል ጉዳተኝነት የሚሰጡ የቋንቋ ድጋፍ ወይም ሌላ ድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚያስፈልግዎት ከሆነ MRCን ያነጋግሩ።

ለራስ በሚመች ፍጥነት በበይነመረብ /ኦንላይን/ የሚሰጥ ሥልጠና ላይ ከእርስዎ የሚጠበቁ ነገሮች

ንቁ ተሳትፎ

  • ለራስ በሚመች ፍጥነት በበይነመረብ /ኦንላይን/ በሚማሩበት ጊዜ በማናቸውም ጊዜ፣ በየትኛውም ቦታ ላይ ሆነው መማር ይችላሉ የበይነመረብ /ኦንላይን/ ትምህርቶች በጊዜ ገደብ የታጠሩ አይደሉም በመሆኑም ትምህርቱን ለማጠናቀቅ የፈልጉትን ያክል ጊዜ ወስደው ማጠናቀቅ ይችላሉ። ለራስዎት የሚያስፈልግዎትን ጊዜ ያክል ይስጡ እና አይጣደፉ። 
  • በአንድ ጊዜ ብዙ ሥራ ከመሥራት መቆጠብ በትምህርቱ ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ያግዝዎታል።
  • የሚቻል ከሆነ ትምህርቱን አንድ ጊዜ ቁጭ ብለው ለመጨረስ ይሞክሩ። ትምህርቱን ላፍታ ማቆም እና በኋላ ላይ እንደገና መመለስ ካስፈለግዎት፣ ለማቋረጥ የሚመች ቦታን ለመምረጥ ይሞክሩ (ለምሳሌ የአንድ ሞጁል መጨረሻ ላይ)።
  • የበይነመረብ /ኦንላይን/ ትምህርቶች በጊዜ ገደብ የታጠሩ ፈተናዎችን መውሰድን ሊጠይቁ ይችላሉ። “በጊዜ ገደብ የታጠረ /proctored/ ፈተና” ማለት ፈተናው የሚሰጠውና ክትትል የሚደረግበት የእርስዎን አፈጻጸም በሚከታተል፣ የእርስዎን ማንነት በሚያረጋግጥ እና በእርስዎ ትምህርት አቀባበል ላይ ተጨባጭ ግብረመልስ በሚሰጥ ሰው የሚሰጥ ፈተና ማለት ነው። 

አካዳሚያዊ የስነ-ምግባር ጥሰት ምንድነው?
አካዳሚያዊ የሥነ ምግባር ጥሰት እርስዎን ወይም ሌላ ሰውን የተለየ ፍትሓዊ ያልሆነ ጥቅም የሚያስገኝ ወይም ሌላ ሰውን ፍትሓዊ ባልሆነ መንገድ እንዲጎዳ ሊያደርገው የሚችል ማናቸውንም ድርጊት መፈጸም ወይም ለመፈጸም ሙከራ ማድረግ ማለት ነው። አካዳሚያዊ የሥነ ምግባር ጥሰትን መፈጸም በጥብቅ የተከለከለ ነው። 

የአካዳሚያዊ ስነ-ምግባር ጥሰት ምሳሌዎች:

መኮረጅ

  • በሚሰጡ ትምህርታዊ መልመጃዎች ላይ የማጭበርበር ድርጊትን መፈጸም ወይም ማታለል። 
  • የተከለከሉ ቁሳቁሶችን መጠቀም (ወይም ለመጠቀም መሞከር)። 
  • ሌሎች የተከለከሉ ቁሳቁሶችን እንዲጠቀሙ ማገዝ። 
  • ሐሰተኛ ወይም አሳሳች መረጃን መስጠት። 

ምሳሌዎች፦ 

  • ሌላ ሰው ለእርስዎ የተሰጥዎት መልመጃ እንዲሠራልዎት ማድረግ ወይም ፈተና እንዲፈተንልዎት ማስደረግ። 
  • የሌላ ሰውን ሥራ መኮረጅ ወይም ለመኮረጅ መሞከር። 
  • የፈተና ጥያቄዎችን ወይም መልሶችን ለሌሎች ማጋራት። 
  • በጊዜ ገደብ የሚሰጥን /proctored/ ፈተና በበይነመረብ /ኦንላይን/ መልቀቅ።

 

የሌሎችን የጥናት ወረቀት ገልብጦ ማቅረብ እና የአእምሮ ሃብት ስርቆት

ምንጩ ከየት እንደሆነ በትክክል ሳይገልጹ የሌላ ሰውን አእምሮዋዊ ሥራ እንደራስ አድርጎ ማቅረብ።

ምሳሌዎች፦ 

  • የሌላ ሰውን ሥራ እንዳለ መገልበጥ እና ልክ የራስ አስመስሎ መጠቀም። 
  • በቤት ሥራ ወይም በፈተናዎች ላይ የሌላ ሰውን ሥራ መጠቀም። 
  • የሌላ ተማሪን መልመጃ ወይም ማስታወሻዎች መስረቅ። 
  • በመምህሩ ተፈቅዶ በይፋ ከመሰጠቱ በፊት የፈተናውን ወይም የመልመጃውን ቅጂ ማግኘት።

 

የሥልጠና ሰነዶችን መነካካትና መቀየር

የሥልጠና ሰነዶችን፣ መልመጃዎችን እና ፈተናዎችን መቀየር።

ምሳሌዎች፦ 

  • በሌላ ሰው ፈተና ወይም መልመጃ ላይ የእርስዎን ስም መጻፍ። 
  • የአሠልጣኙን ፊርማ አስመስሎ መፈረም።

 

ስርቆት ወይም የንብረት ጉዳት ማድረስ

የ SEIU 775 Benefits Group ን ወይም የሌሎችን ተማሪዎች ንብረት መስረቅ ወይም ሆን ብሎ ጉዳት ማድረስ።

ምሳሌዎች፦ 

  • በመማሪያ ክፍሎች ያሉ አቅርቦቶችን ማውጣት። 
  • የሌላ ተማሪን ንብረት መስረቅ ወይም ጉዳት ማድረስ። 
  • የ SEIU 775 Benefits Group ኮምፒውተሮችን፣ ታብሌቶችን፣ ስልኮችን ወይም ሌሎች ዕቃዎችን መስረቅ ወይም ጉዳት ማድረስ።

ከ SEIU 775 Benefits Group የተዋሱዋቸውን መሣሪያዎች ሳይመስሉ መቅረት እንደ ስርቆት ይቆጠራል በመሆኑም የተሳትፎ ዕውቅና ሊያሳጣ እና ሌሎች የዲስፕሊን እርምጃዎችን ሊያስወስድ ይችላል።

 

ቴክኖሎጂ ነክ ጥሰቶች

ኤሌክትሮኒክ መልእክት መላላኪያዎችን እና የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን አላግባብ መጠቀም።

ምሳሌዎች፦ 

  • አይፈለጌ መልእክቶችን መላክ። 
  • የተጋሩ የትምህርት ቤት ሶፍትዌር ፈቃዶችን መጥለፍ፣ ወይም በውሰት ለተገኙ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች SEIU 775 Benefits Group የገባውን የተጠቃሚ ስምምነት የሚጥሱ ተግባራትን መፈጸም።

 

የጥፋት ተባባሪነት

አካዳሚያዊ የሥነ ምግባር ጥሰት ሲፈጸም ከሌሎች ጋር መተባበር።

ምሳሌዎች፦ 

  • ሌላ ተማሪ የእርስዎ ሥራ እንዲኮርጅ መፍቀድ። 
  • ሌላ ተማሪ የአካዳሚ ሥነ ምግባር ጥሰት እየፈጸመ ያለ መሆኑን እያወቁ አይቶ እንዳላየ ማለፍና ለሚመለከተው አካል አለማሳወቅ።

የክፍል ውስጥ ረብሻ

ትምህርትን ማወክ እና ሌሎች ተማሪዎችን መረበሽ።

ምሳሌዎች፦ 

  • ወደ መማሪያ ክፍል ከ10 ደቂቃ በላይ አርፍዶ መድረስ። 
  • ትምህርት እየተሰጠ እያለ ወይም ትምህርቱ በሥርዓቱ ከመጠናቀቁ በፊት ከመማሪያ ክፍሉ አቋርጦ መውጣት። 
  • በትምህርት ክፍለ ጊዜ የግል ወይም የጎንዮሽ ውይይቶችን ማድረግ። 
  • አሠልጣኙ የሚሰጣቸውን መመሪያዎችና ትዕዛዞች አለማክበር።

ጉልበተኝነት፣ ሌሎችን ማዋረድ እና የዘር መድልዎ እና ማግለል ድርጊትን መፈጸም።

በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር በሚከተሉት ላይ ተመርኩዞ ጉልበተኝነትን ማሳየት፣ ሌሎችን ማዋረድ ወይም የዘር መድልዎ እና ማግለል ድርጊትን መፈጸም፦ 

  • ዘር። 
  • ዕድሜ። 
  • የቆዳ ቀለም። 
  • ብሔር። 
  • ጾታ። 
  • የወሲብ ዝንባሌ። 
  • የሥርዓተ ጾታ ማንነት። 
  • የሥርዓተ ጾታ አቋም። 
  • ሃይማኖት። 
  • አገር። 
  • የፍልሰተኝነት ሁኔታ። 
  • የአካል ጉዳተኝነት እና ችሎታ። 
  • የፖለቲካ ዝንባሌ። 
  • ወታደራዊ ታሪክ።
  • ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መደብ።

ምሳሌዎች፦ 

  • አካላዊ እና አካላዊ ያልሆነ ማስፈራራት ወይም በጉልበት መጠቀም። 
  • ዘረኝነትን የሚያሳዩ የአራዳ ቋንቋዎችን፣ ሐረጎችን ወይም ቅፅል ስሞችን መጠቀም። 
  • ተገቢነት የሌላቸውን ምስሎች ወይም ቪዲዮዎች ለሌሎች ማሳየት።
  • ስለ አንድ ሰው ሃይማኖት ወይም ወሲባዊ ዝንባሌ አሉታዊ አስተያየትን መስጠት። 

 

ጥሰቶች እና እንደ ጥሰት ሊታዩ የሚችሉ ድርጊቶች

አንድ ተማሪ ይህን ፖሊሲ ጥሷል ብለው በቀናነት የሚያምኑ ከሆነ፣ ድርጊቱን ለአሠልጣኙ ማሳወቅ ይችላሉ። 

ይህንን ፖሊሲ እርስዎ ጥሰው ከተገኙ ይህንኑ እንዲያውቁት ይደረጋሉ። እንደ ጥሰቱ ሁኔታ በመመርኮዝ፣ ከመጨረሻ ውሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት በቀረበብዎት ክስ ላይ ውይይት ለማድረግ ከመማሪያ ክፍል ውጭ ውይይት ለማድረግ ሊጠሩ ይችላሉ። 

ጥሰትን ወይም እንደ ጥሰት ሊታዩ የሚችሉ ድርጊቶችን ለማሳወቅ፦ 

  • ለእርስዎ አሠልጣኝ ያሳውቁ። 
  • በበይነመረብ /ኦንላይን/ የክስተት ሪፖርት ቅጽ ያስገቡ።
  • MRCን ያነጋግሩ።

ይግባኝ ጥያቄዎች

ይህን አካዳሚያዊ የሥነ ምግባር ደንብ እንደ ጣሱ ተደርጎ በስሕተት ክስ ከተመሠረተብዎት ይግባኝ መጠየቅ ይችላሉ። ይግባኝ ጥያቄ ለማስገባት MRCን ያነጋግሩ። 

የዲስፕሊን እርምጃዎች 

ይህን አካዳሚያዊ የሥነ ምግባር ደንብ እንደጣሱ ከተረጋገጠብዎት፣ እንዲህ ሊደረጉ ይችሉ ይሆናል፦

  • ከመማሪያ ክፍል ያለ ምንም የተሳትፎ ዕውቅና መሰናበት።
  • እንዲህ እንዲያደርጉ ሊጠየቁ ይችላሉ፦ 
    • የሠሩትን መልመጃ ደግመው ሠርተው እንዲያስገቡ።
    • ፈተናን፣ ቴስትን እንደገና እንዲወስዱ ወይም የተማሩትን ትምህርት እንደገና እንዲማሩ።

SEIU 775 Benefits Group ስለፈጸሙት ጥሰት ለእርስዎ ቀጣሪ ሊያሳውቅ ይችላል። አንድ አካዳሚያዊ የሥነ ምግባር ጥሰት ሆን ተብሎ የተፈጸመ እና ለከት ያለፈ አደገኛ ሆኖ ከተገኘ፣ ጥፋቱ በተፈጸመበት ትምህርት ላይ ለነበርዎት ተሳትፎ ሙሉ በሙሉ ዕውቅና ላያገኙ ይችላሉ።

አስፈላጊውን ዝግጅት ያድርጉ 

እባክዎ:

  • አስቀድመው ዕቅድ ያውጡ።
  • የማይረበሹበትን ጸጥ ያለ ትምህርት መከታተያ ቦታ ያዘጋጁ። 
  • በበይነመረብ በሚማሩበት ጊዜ ጸጥታ እንደሚያስፈልግዎት ለቤተሰብ አባላቶችዎ ይንገሩዋቸው።
  • ያልዎት መሣሪያዎች እና የበይነመረብ ግንኙነት ትምህርቱን በሚከታተሉበት ጊዜ በሚገባ ሊሠሩ እንደሚችሉ አስቀድመው ያረጋግጡ። 
  • ወደ መማሪያ ክፍሉ ተመዝግበው ሲገቡ ያልዎትን በመንግሥት የተሰጠ ፎቶ ያለበት ማንነትን የሚገልጽ መታወቂያ ይያዙ። መታወቂያው የስቴት የነዋሪ መታወቂያ ወረቀት፣ የመንጃ ፈቃድ ወይም ፓስፖርት ሊሆን ይችላል።
  • ተመዝግበው ሲገቡ ማይክራፎኑን አያስተካክሉት። በራስሰር /በአውቶማቲክ/ ድምፀ ከል ይሆናል። ጥያቄ ሲጠይቁ ወይም መልስ ሲሰጡ ራስዎት ድምፀ ከሉን ማንሣትና መናገር ይችላሉ፣ ሆኖም ግን በትምህርት ሂደቱ ላይ እርስዎ በማይናገሩበት ጊዜ ሁሉ መልሰው ድምፀ ከል ማድረግዎን አይዘንጉ።
  • ፕሮግራሙን የሚመራው የእርስዎን ፊት በግልጽ እንዲታየው የእርስዎን ካሜራ ያብሩት እና ትምህርቱ እስኪያልቅ ድረስ ካሜራዎን እንደበራ ይተዉት። የሌሎችን ግላዊነት ለመጠበቅ ሲባል፣ በካሜራው ውስጥ የሚታዩት ግለሰብ እርስዎ ብቻ መሆንዎትን ያረጋግጡ (ምንም ዓይነት ቤተሰብ አባል፣ ጓደኞች፣ ደንበኞች ወይም ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት በካሜራው መታየት የለባቸውም)።
  • የቋንቋ እገዛ , ለአካል ጉዳተኝነት የሚሰጡ አገልግሎቶች ወይም ሌላ ድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችንማግኘት የሚያስፈልግዎት ከሆነ MRCን ያነጋግሩ።
  • የእርስዎን የግልዎን ተመዝግቦ መግቢያ መረጃ ለሌላ ለማንም አሳልፈው አይስጡ።

በቨርቹዋል የሚሰጥ ሥልጠና ላይ የሚጠበቁ ነገሮች:

ንቁ ተሳትፎ

እባክዎ:

  • ለተሳትፎዎ ዕውቅና እንዲያገኙ ሙሉ የትምህርት ክፍለ ጊዜውን ተምረው ያጠናቁ። 
  • የእርስዎን ካሜራ ያብሩ፣ በጽሑፍ በሚደረግ ውይይት ወይም በቡድን ውይይቶች ላይ ይሳተፉ እንዲሁም ጥያቄ ሲቀርብልዎት መልስ ይስጡ። ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚጠበቅብዎትን ያክል ሳይሳተፉ ቢቀሩ ማግኘት የሚገባዎትን የዕውቅና ማረጋገጫ ላያገኙ ይችላሉ።
  • ካሜራዎን ማጥፋት የሚያስፈልግዎት ሁኔታ ከተፈጠረ ለአሠልጣኙ/ፕሮግራም መሪው በግል በሚላክ የጽሑፍ መልእክት አስቀድመው ያሳውቁ። በጽሑፍ መልእክት መላላኪያው በመጠቀም ትምህርቱ እስኪጠናቀቅ በንቃት ተሳትፎ ማድረግዎን እባክዎ ይቀጥሉ።   
  • መዝግቦ ለማስገባት እና መዝግቦ ለማስወጣት የፕሮግራሙ መሪ መረጃ እንዲሰጠው ሲጠይቅ ምላሽ ይስጡ።
  • ንቁ ሆነው በትኩረት እስከ መጨረሻው ትምህርቱን ይከታተሉ። በግልጽ በሚታይ ሁኔታ እንቅልፍ እንዳሸነፋቸው፣ መኪና እየነዱ ወይም በእግራቸው እየሄዱ እንደሆነ የሚታዩ ተማሪዎች ከመማሪያ ክፍሉ ይሰናበታሉ እንዲሁም ሌላ ክፍለ ጊዜ እንዲያዝላቸው እንዲጠይቁ MRCን እንዲያነጋግሩ ይጠየቃሉ።
  • በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ላይ መወያየትን ይቀጥሉ። ከትምህርቱ ጋር ግንኙነት በሌለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ማውራት ከጀመሩ እና ንግግርዎን እንዲያቋርጡ ከተነገርዎት በኋላ መናገርዎን ከቀጠሉ፣ ከክፍሉ ይሰናበቱ እና ሌላ ክፍለ ጊዜ እንዲያዝልዎት MRCን እንዲያነጋግሩ ይጠየቃሉ።
  • በማናቸውም ጊዜ አሠልጣኞችን፣ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን እና ሌላ ተማሪዎችን በአክብሮት ያስተናግዷቸው።
  • ተራዎ እስከሚደርስ ይጠብቁ እንዲሁም ሌሎች ሲናገሩ ያዳምጡዋቸው።
  • ልክ በግል በአካል እንደሚሰጥ ትምህርት ሁሉ በኮምፒውተር /ቨርቹዋል/ በሚሰጠው ትምህርት ተመሳሳይ ጊዜ ሊያጠፉ እንደሚችሉ ዐውቀው ከወዲሁ ይዘጋጁበት። በኮምፒውተር የሚሰጡ /ቨርቹዋል/ ትምህርቶች ልክ በግል በአካል እንደሚሰጡ ትምህርቶች ሁሉ እኩል ተሳትፎ ማድረግን ይጠይቃሉ። 

በሰዓቱ ሳያረፍዱ መድረስ እና ሌሎች በክፍል ተገኝቶ የመማር ግዴታዎች

እባክዎ:

  • በሰዓቱ ሳያረፍዱ ተመዝግበው ይግቡ እና ከዕረፍት እና ከምሳ በኋላ በሰዓቱ ይመለሱ። ወደ ትምህርቱ ከ10 ደቂቃ በላይ አርፍደው ከደረሱ፣ ወደ ኮምፒውተር /ቨርቹዋል/ መማሪያ ክፍሉ እንዲገቡ አይፈቀድልዎትም እንዲሁም ለዚህ የቀሩበት ክፍል የተሳትፎ ዕውቅና አያገኙም።
  • የተሳትፎ ዕውቅና ማግኘት እንዲችሉ ከትምህርቱ መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ የራስዎትን ማንነት ይግለጹ። የፕሮግራሙ መሪ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት እና ከትምህርቱ መጨረሻ ላይ የተማሪዎችን ስም ይመዝግባል። 
  • በመማሪያ ክፍል ተገኝቶ ለመማር የማይችሉ ከሆነ በተቻለ ፍጥነት ለ MRC ወይም ለእርስዎ ኤጀንሲ የሥራ ቀጣሪ ያሳውቁ። MRC ወይም የእርስዎ ኤጀንሲ የሥራ ቀጣሪ ማናቸውንም ያመለጥዎትን ትምህርት በሌላ ክፍለ ጊዜ ተገኝተው ማካካስ የሚችሉበትን መንገድ በማዘጋጀት ላይ ሊያግዝዎት ይችላሉ።

የግል ስልኮች

እባክዎ:

  • በትምህርት ወቅት የእርስዎን የእጅ ስልክ ድምፅ ያጥፉት። 
  • ትምህርት እየተሰጠ እያለ የስልክ ጥሪዎችን አያድርጉ ወይም የጽሑፍ መልእክት አይላላኩ።
  • የግል የስልክ ጥሪዎችን ለማድረግ ሆነ ለመቀበል ወይም ሌላ የግል ጉዳዮችን ለማከናወን በመርሐ ግብሩ ላይ የተቀመጡትን የዕረፍት ጊዜዎችን ወይም የምሳ ሰዓትን ይጠቀሙ።

የስልጠና ደረጃዎች

ለተለያዩ ሰራተኞች የስልጠና ደረጃዎች ይለያያሉ። የትኛዎቹ ኮርሶች ለእርስዎ ተገቢ እንደሆኑ እንዲወስኑ የሚያግዝዎ መመሪያ አለን።

ተጨማሪ ይወቁ